ከባለጸጋው ሽማግሌ
ተረት ተረት
ከብዙ ዓመታት በፊት አንድ ባለ ፀጋ ሰው ሰባት ወንድ ልጆች ነበሩት:: እጅግ የተትረፈረፈ ሀብት ነበረው ዕድሜውም በገፋ ጊዜ ለሰባቱ ወንድ ልጆቹ መሬት ገዛላቸው:: ከዚያም በሕይወቱ በሚገባ ተደሰተ ፣ የቀረውን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ለራሱ ተጠቀምብት ፤ እንዲሁም ጎረቤቶቹን በሙሉ ግብዣ ጋበዛቸው። ወዳጆቹም "ለልጆችህ ገንዘብ ማስቀመጥ አለብህ!" አሉት። እርሱም "በልጆቼ ዕድልና ብልህነት እተማመናለሁ!" ብሎ በኩራት መለሰላቸው።
ልጆቹ ግን በጣም ሰነፍ ስለነበሩ መሬታቸውን ምንም አላረሱም ነበር። አባታቸው ሲሞት አርባ ቀን ጠበቁ፤ ከዚያም አባታቸው ገንዘቡን ያስቀምጥበት የነበረውን ሳጥን ከፈቱ። ይሁን እንጂ በውስጡ ያገኙት አንድ ደብዳቤ ብቻ ነበር። በደብዳቤውም ላይ አባትየው እንደዚህ ብሎ ጽፏል "በሰጠዋችሁ መሬት ውስጥ ሁሉ ወርቅ ታገኛላችሁ" ነገር ግን ልጆቹ ባነበቡት ነገር በጣም አዘኑ ምክንያቱም ብዙ ገንዘብ ለመውረስ ተስፋ አድርገው ነበርና። በመጨረሻም ታላቅ ወንድማቸው እንደዚህ አላቸው "በእያንዳንዱ መሬት ውስጥ ወርቅ ካለ? ወርቁን ለማግኘት ማሳውን መቆፈር አለብን።" ወንድሞቹም በዚህ ተስማምተው መሬቱንም በየተራ መቆፈር ጀምሩ፤ ሆኖም ግን ምንም አይነት ወርቅ ሊያግኙ አልቻሉም። ታናሽ ወንድማቸው በጣም በተዳከመ ድምጽ "ምንም ነገር አላገኘንም፤ በመሆኑም ዕድላችንን ሌላ ቦታ በመሄድ፣ በግብርና ተቀጥረን ብንሠራ ይሻላል" አላቸው። እነሱም ከታላቅ ወንድማቸው በስተቀር በሃሳቡ ተስማምተው መንደራቸውን ለቀው ተሰደዱ::
መሬቱ በሙሉ እንደ አዲስ የተቆፈረ በመሆኑ ታላቅየው ገብስ ዘራበት። መሬቱ ድንግል ስለነበረ የዘራው ሁሉ በጣም ከማደጉ የተነሳ የተትረፈረፈ ምርት ሰበሰብ በርካታ ጎተራዎችንም ሞላ። እህሉን ሸጦ ተጨማሪ እርሻዎችንም ገዛ። ብዙም ሳይቆይ በጣም የታወቀ ሀብታም ገበሬ ለመሆን ቻለ።
በተቃራኒው ሌሎቹ ወንድሞቹ አነስተኛ ገንዘብ ለማግኘት በባዕድ ሰዎች እርሻ ላይ ጠንክረው መሥራት ነበረባቸው። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እርስ በርሳቸው "ሕይወት በጣም አስቸጋሪ ነው እስቲ ወደ መንደራችን ተመልሰን ወንድማችን ምን እንዳጋጠመው እንመልከት" ብለው ወደ ቀያቸው ጉዞ ጀመሩ። በጣም ተርበው፣ አቧራማና የተቀዳደደ ልብስ ለብሰው ወደ መንደራቸው ደረሱ። የወንድማቸውን በር አንኳኩ፤ ወንድማቸውም ከመጎሳቆላቸው የተነሳ አላወቃቸውም ነበርና እንድዚህ አሉት "እኛ ወንድሞችህ ነን! ብዙ ስራ በትንሽ ዋጋ እየስራን ፤ ብዙ መከራ ደርሶብናል ። ንገረን፤ ወርቁን አገኘኸው?"
ታላቃቸውም፣ ወንድሞቹን ወደ ቤት አስገባቸው፣ ቅያሪ ልብስ ሰጣቸው ምግብ እና መጠጥም አቀረበላቸው። ከበሉ እና ከጠጡ በኋላ ታላቅ ወንድማቸው እንዴት እንደዚህ ባለሀብት ሊሆን እንደቻለ ማስረዳት ጀመረ። እንዲዚህም አላቸው "አባታችን ወርቅ ማለቱ በጣም ለም የነበረውን የእርሻ መሬት ማለቱ ነበር። ተመልከቱ መሬቱ ብዙ ሃብት አምጥቶልኛል። ከዛሬ ጀምሮ ላካፍላችሁ እፈልጋለሁ።" ከዚያን ቀን ጀምሮ ሰባቱ ወንድማማቾቸ በእርሻው ላይ በጋራና በትጋት በመስራት እንደ አባታቸው ባለጸጋ ለመሆን ቻሉ።
ተረቴን መልሱ አፌን በዳቦ አብሱ።
እትም በጃሚላ ጄኒኬ፣ ከ ሲ. ዴትልፍ፣ ጂ. ሙለር፣ ኢትዮጵያዊ ተረት፣ ሙኒክ 1992 ©ሙታቦር ተረት ፋውንዴሽን